ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በአውስትሪያ በተፈጸመ የጅምላ ተኩስ የተገደሉትን በጸሎት አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ረቡዕ ሰኔ 4/2017 ዓ. ም. ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት በአውስርቲያ ግራዝ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት የተገደሉትን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ በአደጋው የሞቱትን ልጆች ነፍስ እግዚአብሔር ወደ ሰላሙ እንዲቀበላቸው ከቤተሰቦቻቸው፣ ከአስተማሪዎቻቸው እና ከጓደኞቻቸው ጋር በመተባበር በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።
ማክሰኞ ሰኔ 3/2017 ዓ. ም. ማለዳ፥ አንድ የ21 ዓመት ወጣት በድሬየርሹትዘንጋሴ የሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪ በከፈተው ተኩስ አንድ ጎልማሳን ጨምሮ 10 ሰዎች ሲሞቱ በደርዘን የሚቆጠሩ ቆስለዋል። ይህ ጥቃት በአውስትሪያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከተፈጸሙት መካከል የከፋ እንደሆነ ተነግሯል።
ይህን በማስመልከት አገሪቱ ሦስት ብሔራዊ የሐዘን ቀናትን ማወጇን የትምህርት ቤቱ ቻንስለር ክርስቲያን ስቶከር ገልጸው፥ አደጋውን በማስመልከት ሲናገሩ፥ “በአገራችን ታሪክ የጨለማ ቀን፣ የማይታሰብ ጥቃት እና ሁላችንንም ያስደነገጠ አደጋ” ሲሉ ገልፀውታል።
ጥቃቱን ተከትሎ በርካታ የአውሮፓ መሪዎች ሐዘናቸውን ገልጸዋል። የአውሮፓ ኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን፥ “ትምህርት ቤቶች የወጣትነት፣ የተስፋ እና የወደፊት ተምሳሌት መሆን ይገባቸዋል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ “ትምህርት ቤቶች የሞት እና የጥቃት ቦታዎች ሲሆኑ መመልከት ከባድ ነው” ሲሉ አክለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ወ/ሮ ካጃ ካላስ በክስተቱ የተሰማቸውን ድንጋጤ ገልጸው፥ “እያንዳንዱ ሕጻን በትምህርት ቤት ውስጥ ደኅንነት ሊሰማው፣ ከፍርሃት እና ከጥቃት ነፃ ሆኖ መማር አለበት” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።