ፈልግ

አንድ ዩክሬናዊ በሩሲያ ወረራ ወቅት የተጣሉ በደርዘን የሚቆጠሩ ፍየሎችን ሲያስጠልል አንድ ዩክሬናዊ በሩሲያ ወረራ ወቅት የተጣሉ በደርዘን የሚቆጠሩ ፍየሎችን ሲያስጠልል   (ANSA)

ካርዲናል ፓሮሊን፥ ጦርነትን በማስቀረት ሰላምን መፍጠር የሚቻል መሆኑን አስገነዘቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን “ላ ስታምፓ” ከተሰኘ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ቅድስት መንበር ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ገልጸው፥ ጦርነትን መደበኛ በማድረግ የትጥቅ ትግልን መፍትሔ አድርገው የሚያስቡትን አስጠንቅቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊው፥ በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት በማስመልከት በቱርክ መዲና ኢስታንቡል ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት በመቋርጡ ምክንያት የተቀሰቀሰው ሁከት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።


“በኢስታንቡል ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት አለመሳካቱ ጦርነትን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ሊገታው አይችልም” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ “ቅድስት መንበር ዛሬም ለሰላም ላላት ተልዕኮዋ ታማኝ በመሆን፥ ጦርነት የማይቀር እንደሆነ የሚወስድ የተሳሳተ አስተሳሰብ የመቃወም ጥሪዋን ታድሳለች” ብለዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን አክለውም፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቁርጠኝነት በማስታወስ እና ቃላቶቻቸውንም በመጥቀስ፥ “ይህ ሰላም እንዲስፋፋ ሁሉንም ጥረት አደርጋለሁ” ማለታቸውን አስታውሰው፥ “ጠላቶች ፊት ለፊት እንዲገናኙ፣ ተስፋ እና ሰላም ወደ ሕዝቦች እንዲመለስ ለማድረግ ቅድስት መንበር የዘወትር ጥረቷን ትቀጥላለች” ሲሉ ተናግረዋል።

በዩክሬን ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ማምጣት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በዩክሬን ውስጥ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያለማቋረጥ ጥሪ ማቅረባቸውን እና ይህ ምን ማለት እንደሆነ በተጨባጭ የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፡- በግድ የተጫኑ መፍትሄዎች ወይም የማስፈራራት ውጤት ከሆነ እውነተኛ ሰላም ሊመጣ አይችልም። ነገር ግን እውነተኛ ሰላም ሊመነጭ የሚችለው በመከባበር እና በውይይት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ሰላም፥ ውርደትን ሳያስከትል እና ቁስልን ሳይፈጠር ነገር ግን የሚመለከታቸውን አካላት ክብር የሚጠብቅ መሆን አለበት” ሲሉ አስረድተው፥ ሰላም ጸንቶ ሊቀጥል የሚችለው በጦር መሣሪያ ኃይል በተገኘ ደካማ አካሄድ ሳይሆን ነገር ግን በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በፍትሕ፣ በነፃነት እና በጠንካራ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” ብለዋል።

የአውሮፓ የጦር መሣሪያ ውድድር እና ራስን የመከላከል ገደቦች

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በአውሮፓ ውስጥ እየጨመረ የመጣው ወታደራዊ ወጪ ያስከተለውን አለመረጋጋት እና ስጋት በማስመልከት ሲናገሩ፡- “እያንዳንዱ ሀገር ሉዓላዊነቱን እና ደህንነቱን ማስጠበቅ ሕጋዊ እና አስፈላጊ ቢሆንም፥ ወታደራዊ አቅም መገንባት በአገሮች መካከል ምን ያህል መተማመንን እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ይረዳል?” ብለን መጠየቅ አለብን ብለዋል።

ከመጠን ያለፈ የጦር መሣሪያ ክምችት እና ውድድር ፍርሃትን በመቀስቀስ በሁሉም ላይ ከባድ መዘዝን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። “ራስን የመከላከል መብት ፍጹም አይደለም ያሉት” ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “የግጭት መንስኤዎችን ከመቀነስ እና ከተቻለም ከማስወገድ ግዴታ ጋር መያያዝ አለበት” ብለዋል።

በጋዛ ውስጥ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የጋዛን ሁኔታ በማያሻማ መልክ ሲገልጹ፥ “ጋዛ ውስጥ ሲቪሎች ለከፍተኛ ሰብዓዊ አደጋ ተጋልጠው በሚገኙበት ባሁኑ ወቅት በጋዛ ምን እየተካሄደ እንዳለ መነጋገር ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

ጦርነት ችግሮችን የመፍቻ መንገድ ሊሆን እንደማይችል በመግለጽ፥ የእስራኤል መንግሥት ወደ ጋዛ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይገባ ያስቀመጠውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ አሳስበው፥ ቫቲካን በድርድር የሚገኙ መፍትሄዎችን መደገፏን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

ከ140 በላይ ታጋቾች እንዲለቀቁ ያደረጉ ሁለቱ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ይህም ድርድሩ እጅግ ውስብስብ በሆነ አውድ ውስጥ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

የእስራኤል-ቫቲካን ግንኙነት እና የአይሁድ-ክርስቲያን የጋራ ውይይት

የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መመረጥን በማስመልከት በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ መገኘታቸው በግዛቶች መካከል የተፈጠረውን ፈጣን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያሳይ እንደሆን የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ቅድስት መንበር ለማንም በሯን ዘግታ አታውቅም” ሲሉ አረጋግጠዋል።

አክለውም፥ የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ የግዛቲቱ ፕሬዚዳንት፥ ከሃይማኖት ይልቅ የፖለቲካ ዓላማን የሚያራምዱ መሆናቸውን በማስረዳት፥ ቅድስት መንበር ተስፋ የምታደርገው በሁለቱ መንግሥታት መካከል ፍትሐዊ እና ዘላቂ የሰላም ሂደትን ለማስፈን እና የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ እንደሆነ አስረድተዋል።

ብጹዕነታቸው በተጨማሪም፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፀረ-ሴማዊነት ላይ የነበራቸውን ጠንካራ እና ተከታታይ አቋም በማጉላት፥ አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአይሁድ እና በክርስትና እምነት መካከል ያለውን ግንኙነት ማሳደግ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

አዲሱን ቀዝቃዛ ጦርነት ማስወገድ

እያየለ ስለሚመጣው የአሜሪካ እና ቻይና ውጥረት የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በቀዝቃዛ ጦርነት አስተሳሰብ ውስጥ መውደቅ እንደማይገባ አስጠንቅቀው፥ “እነዚህ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳይሸጋገሩ ለማድረግ ውይይት ብቸኛው አዋጭ መንገድ እንደሆነ የቅድስት መንበር እምነት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ዋሽንግተን እና ቤጂንግ ገንቢ ንግግሮችን በማድረግ እና እንደ ንግድ እና ደህንነት ባሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፈለግ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ግጭትን ወይም ጦርነትን እንደ ብቸኛ አማራጭ የማየት አደጋን ማስወገድ አስፈላጊ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ሌሎች አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በብዝሃነት ላይ ኢንቨስት በማድረግ ሚዛናዊ ብዝሃነትን እንዲከተሉ ጥሪ በማቅረብ፥ ዲፕሎማሲ፣ እርስ በርስ መከባበር፣ ፍትህ እና ግልጽነት፥ ሁሉንም ዘላቂ ሰላም እና ልማት የሚያበረታቱ መፍትሄዎችን ለመፈለግ ወሳኝ መሣሪያዎች እንደሆኑ በመግለጽ ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።

ለሰላም የቆመ ታማኝ ድምፅ

በቅርቡ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሹመት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ዓለም አቀፍ መሪዎችን በማስመልከት ሲናገሩ፥ “ይህ ቅድስት መንበር ለሰላም ባላትን ቁርጠኝነት ዓለም አቀፍ እውቅናን ያገኘችበትን የሚያሳይ ትልቅ ምልክት ነበር” በማለት የቫቲካን ዲፕሎማሲያዊ ሚናን አረጋግጠዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ቀደም ሲል በሐዋርያዊ አገልግሎት ሥልጣን መጀመሪያ ላይ፥ የመገናኛ ድልድዮችን በጋራ ለመገንባት አስቸኳይ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰው፥ “ይህም በዓለም መሪዎች መካከል ፍላጎት እና ገንቢ ውይይት እንዲፈጠር አድርጓል” ሲሉ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል።

 

04 Jun 2025, 17:10